Wednesday, August 7, 2013

ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ የፀረ ሽብር ህጉን የመቃወም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከእስር ቤት ሆና ባስተላለፈችው መልዕክት ጠየቀች

576820_643438789017118_1777115518_nነሀሴ ፩ ቀን ፩፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሰኔ 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ እየተካሄደ ያለው የፀረ ሽብር ህጉን የመቃወም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከእስር ቤት ሆና ባስተላለፈችው መልዕክት ጠየቀች፡፡
ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ጋዜጠኛ ርዩት አለሙ ገዥው የኢህአዴግ መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን ለስልጣኑ ማራዘሚያነት ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ገልጻ እየተደረጉ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎችና ሌሎችም ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጻለች፡፡
የተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹ በዋናነት ኢህአዴግ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው እምነቷ እንደሆነ የተናገረችው ጋዜጠኛ ርዮት በፀረ ሽብር አዋጁና አተገባበሩ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ለቁጥር የሚያዳግቱ የኢትዮጵያውያ ችግሮች ምንጩ ራሱ ኢህአዴግ እንደሆነ ተናግራለች፡፡
ኢህአዲግ ስልጣኑን ለማራዘም የሚረዳ እስከመሰለው ድረስ ማንኛውንም ዓይነት ተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ የማይል መሆኑን እስኪያንገሸግሸን ታዝበናል የምትለው ጋዜጠኛ ርዮት የኢህአዴግ ድርጊቶች ሁሉ ምክንያቶቹ ከዘረኝነት፣ ከስልጣን ጥመኝነት፣ ካለ አግባብ ከመበልጸግና ከመሳሰሉት እኩይ ፍላጎቶች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
ከኢህአዴግ መልካም ነገር አይጠበቅም ያለችው ርዮት የትኛውንም አይነት የሰለጠነና ሰላማዊ ትግል የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በመክፈል ስርዓቱን መለወጥ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ባስተላለፈችው መልዕክት ገልጻለች፡፡
ስለ ስርዓቱ መለወጥ ሲታሰብ ግን ኢህአዴግ ያስቀመጣቸውን በየዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ርዮት አለምና በጥቅም የመከፋፈል እንቅፋቶችና በጥልቀት አስቦ መንቀሳቀስ ግድ ይላል ብላለች፡፡
በየአቅጣጫው የተበታተኑ እንቅስቃሴዎችን ከማካሄድ ይልቅ በህብረት ሆነን መታገል መቻል ይኖርብናል ስትል መልዕክቷን ያስተላለፈችው ርዮት ከኢህአዴግ በኋላ ስለሚመሰረተው ስርዓትም በደንብ ማሰብና መመካከር የሀገሩ ጉዳይ ይመለከተኛል ከሚል ማንኛውም ሀላፊነት ከሚሰማው ዜጋ በተለይም ደግሞ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ከሚመሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ይጠበቃል ብላለች፡፡
ርዮት አለሙ በሰኔ 2003 ዓ.ም. የሽብር እንቅስቃሴ ለማድረግ ተንቀሳቅሰሻል በሚል ነበር በፀረ ሽብር ህግ ተከሳ የ14 ዓመት እስር ፍርድ የተፈረደባት ይግባኝ በመጠየቋም የእስር ቅጣቷ ወደ አምስት ዓመት ተቀንሶላት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከሌሎች የህግ ታራሚዎች ጋር ትገኛለች፡፡
አለም አቀፍ የሴቶች የሚዲያ ፋውንዴሽን ጋዜጠኛ ርዮትን የ2005 በጋዜጠኝነት ትጋትን ካስመሰከሩ በማለት የሸለማት መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment