Sunday, August 11, 2013

በውኑ መንፈስ ይታሰራልን?

suffering-620x148eskinder[1]
(በየነ መስፍን ከጀርመን)
August 10, 2013
እንደ ህወሃት አይነት አምባገነን መንግስታት ከተጠናወታቸው በርካታ ችግሮች መካከል ትግል እና ታጋይን ነጣጥሎ ያለማየት ችግር ሲሆን የትግል መሰረቱ ፍትህ እስከሆነ ድረስ፣የትግል መዳረሻው በተፈጥሮ የተገኘን መብት በችሮታ ካልሰጠናችሁ ከሚሉ አምባገነኖች መዳፍ ፈልቅቆ ለማውጣት እስከሆነ ድረስ በእርግጥም ይህ ትግል ከስጋና ከደም በላይ የተሻገረ በብዙሃን ላይ የሚሰርፅ መንፈስ ነው።ስለሆነም እንደመንፈስ የረቀቀው ትግል በታጋዩ ላይ ገዝፎ ይገለጥ ይሆናል እንጂ ታጋዩ ቢሰዋ አልያም በአምባገነኖች የግዞት እስር ቢወረወር ትግሉ አይታሰርም ደግሞም አይሞትም።
ለምሳሌ ፀረ-አፓርታይድ ትግል ማጠንጠኛው ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህን መሻት እንዲሁም የዘረኝነትን ክፉ ቀንበር መሰባበር ነበር።
ነገር ግን በወቅቱ የነበሩ የዘረኛው አፓርታይዳዊ አገዛዝ አመራሮች የትግሉን ረቂቅ ወጣቶችንና አዛውንቶችን ለእስርና ለሞት ከመዳረጋቸው ባሻገር የትግሉን መሪ ኔልሰን ማንዴላን በሮበን ደሴት ላይ ለ27 ዓመታት ሊያስሩ ችለዋል።ይሁን እንጂ የትግሉ መንፈስ ፍትህና ነፃነትን የሚፈልጉትን ሁሉ ኮርኩሮ የመቀስቀስ አቅም ስለነበረው ፀረ-አፓርታይድ ፍልሚያው እንደ ሰደድ እሳት ከያቅጣጫው ይንቀለቀል ነበር።ይልቁንም ታጋዮችን በመስበር ትግሉን እናከስማለን የሚሉትን አምባገነኖች የትግሉ ወላፈን እየበላቸው ዛሬ ከመጥፎ ተሞክሯቸው ጋር ታሪክ ሆነው ቀርተዋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያም እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ከዚህ ብዙም የሚርቅ አይደለም።ታጋዮችን ላነሳሳቸው የህዝብ ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ በግለሰቦች ላይ የሚደረገው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ቢመጣም የትግሉ እቶን ይበልጥ ከመንደድ ወደኋላ አላለም።ሠርካለም ፋሲል በግፍ በወህኒ እንድትወልድ መደረጉ እነ ርዕዮት አለሙን ከጋዜጠኝነት አላሸሻቸውም፥ይልቁን ስለእውነት እና ፍትህ በመቆም ለብዙ ወጣቶች አርአያ በመሆን የወያኔን የግፍ ፅዋ በወኔ ተጎነጨችው እንጂ።እስክንድር ነጋን በግፍ በህፃን ልጁ ፊት በካቴና በማሰር ወደ ወህኒ ሲጋዝ፣በውርስ ያገኘውን የእናቱን ቤት መንግስት ሲወርሰው በርግጥም በወያኔ ሹማምንት ስሌት ”እስክንድርን ያየ ይቀጣ” በሚል የህዝብ የነፃነት ጥያቄ በፍርሃት ካባ ተሸፍኖ ይቀራል ከሚል የመነጨ ነበር።
በቀለ ገርባን በማሠር፣ባለቤቱን በግፍ ከሥራ በማፈናቀል የተተኪው ትውልድ አካል የሆኑ ህፃናት ልጆቹን ለችግር በማጋለጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የነፃነት ጥያቄ ማፈን አይቻልም።ይልቁን ዛሬ የትግሉ መንፈስ አድማስን ተሻግሮ የነፃነት ጩኸታችንን በአውሮፓ እና በአሜሪካ መንግስታት ተወካዮች ሳይቀር እየተስተጋባ ይገኛል።በቅርቡ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ አባላት በጀርመናዊቷ ባርባራ ሎክቢለር በመመራት ወደ አዲስ አበባ ያቀና ሲሆን በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብዓዊ መብት አያያዝ አሳሳቢ መሆኑን የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ሁኔታ ለማየት ወደ ቃሊቲ እንዲሄዱ ከተደረገ በኋላ በተለመደው የወያኔ ድራማ ከስፍራው ያለ ውጤት እንዲመለሱ ተደርጓል።
በአንድ ነገር ይበልጥ እርግጠኞች ነን፦እልፎች በወያኔ ግዞት በግፍ ሊጣሉ ይችላሉ፣ አዕላፍት ሊሰው ይችላሉ። ነገር ግን የትግላችን መሠረት የሆነው የነፃነት፣የእኩልነት፣የፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፣የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ፍትህ ጥያቄያችን ግን ፈፅሞ በግዞት በቃሊቲና መሰል ወኅኒዎች ሊታሠር አይችልም።
ጸሃፊው በዚህ አድራሻ ይገኛሉ: beyenemesfin77@yahoo.com

No comments:

Post a Comment