Wednesday, June 5, 2013

ዶ/ር አበራ ጀምበሬ ትዝታዬና መጽሐፉ

ከመዝገብ ቤት ሠራተኛነት እስከ ሚንስትሮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊነት (ወለላዬ ከስዊድን)
aberaa


ዛሬ ብቻ ኖረው – በዛሬ ያልቀሩ
ነገንም አስበው – ለነገ የሠሩ
ለራሳቸው ሳይሆን – ለህዝብ የኖሩ
ግዴታ ሆነና ሞት – ቢሆን ዕጣቸው
ሲበራ ይኖራል – አይጠፋም ሐቃቸው
ግጥም - አስራት ዳምጠው
abera
ዶ/ር አበራ ጀምበሬ
በስድስተኛ ዓመቴ መጨረሻ ግድም አንድ ቀይ እንግዳ እቤታችን መጣ። ከናትና አባቴ ጋር ሆኜ ከሰውየው ጋር የመቀመጥ እድል አገኘሁ። ቀዩ ሰውዬ ሳቂታ ፊት፣ የሚቁለጨለጩ አይኖች፣ ሰልካካ አፍንጫና፣ የሞሉ ጉንጮች አሉት።ያም ሆኖ ሙሉ ፊቱ ስትታይ አነስተኛ ነች።
ይህን ሰው ከዛን ቀን በፊት ስለማወቄ እርግጠኛ አይደለሁም። እንኳን እሱን ሌሎች አብረውኝ ያሉትንም ዝምድናቸውን ለይቼ ለመናገር እቸገራለሁ። ያን ቀን ያንን ሰው አይነ ህሊናዬን ምን እንዳበራው አላውቅም ቀረብኩት። አንድ አይነት የሚያስተሳስረን ነገር እንዳለን ገባኝ። ነፍስ ማወቅ ይሄ ይሆን? ይሄ ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችል?
ከዛ በፊት ያለውን ምኑንም የማላውቅበት እድሜዬ በኔ ላይ መቆጠሩ ይቆጨኛል። እንዴ! ምኔን እስከምናምኔ ጠራርገው ያኖሩኝ እያሉ እንዴት አድርጎ ነው ያ እድሜ በኔ ላይ የሚቆጠር? ለሚሰጡት ይስጡ እንጂ ያ የእድሜ ዓመት የኔ አይደለም።
እንደውም ያኔ የሚሉት ልጅ እኔ መሆኔን እጠራጠራለሁ። “ሀይለኛ ነበርክ” ይሉኛል ። እናቴን ስንት ልጅ ወለዱ? ሲሏት እንደቀኑ ያበጣበጤ ሁኔታ አንድ እራሴን አራትም አምስትም የምታደርገኝ ጊዜ ነበር አሉ። ታዲያ አሁን እንዲህ የበረድኩ ዝምተኛና ኮሽ የማይልብኝ ሰው እንዴት አድርጌ ያን ልጅ ልሆን እችላለሁ? እንጃ!
አንድ ቀን ከዛ ቀይ ሰው ጋር አብሬ ቁጭ ብያለሁ። አሁን በደንብ አውቄዋለሁ። ለነገሩ ማን ልብ ይበልልኝ እንጂ ፎቶው እቤታችን በትልቁ ተለጥፎ ከርሟል።
አሁን እያዋራኝ ነው። የተለመደች ንግግራችንን ቀጥለናል። ዜማ ባላት አባባል ጋሽዬ … ጋሽዬ … በማለት ጀመረ
“አቤት! አቤት! …”
“የት ይኖራል?”
“ጌታ ቤት”
“ምን ይበላል?”
“ፍትፍት”
“ምን ይጠጣል?”
“ወተት”
“የት ይተኛል?”
“ግርጌ”
“ምን ይለበሳል?”
“ቡትቶ”
“እህህ …”
“ይነቀኝ! …”
ይቺ የዘወትር ንግግራችን ናት። እናቴ ነበረች ያስለመደችኝ። ከዚህ በኋላ ጥያቄዬ አያቋርጥም። ሆፕ አድርገኝም አለ … በቀላሉ መላቀቅ የለም። ሲወጣ ሱሪውን ጨምድጄ እሪ ነው። በስንት ኡኡታ ነበር የሚሄደው። ያውም ቸራልያ ብስኩት ከሰዓት ከረሜላ ጋር ሊያመጣ ቃል ገብቶ።
በዚህ አይነት ሁኔታ ተለማምደን እንደቆየን እንዴት እንደሆን ባላወኩት ምክንያት ከቤተሰባችን ጋር ከአዲስ አበባ ለቀን ወጣን። ከዛ ቀይ እንግዳም ለረጅም ጊዜ ተለያይተን ከረምን።
በሚቀጥለው ጠቅልለን ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ ትልቅ ልጅ ሆኛለሁ ማለት ይቻላል። ከአምስተኛ ወደ ስድስተኛ ክፍል ያለፍኩባትን የምስክር ወረቀት ይዤ ነበር። አንድ ቀን ከምጫወትበት ወደቤት ተጠርቼ ስመጣ 27894 አ.አ. የሚል ታርጋ የለጠፈች ሰማያዊ ማርቸዲስ እቤታችን ግቢ ቆማ አየሁ። እንግዳውን ለማየት አልቸኮልኩም። መኪናዋን ወደድኳት፣ ዞርኳት፣ ነካኋት፣ ያላደረኳት ነገር የለም። የሳምኳት ሁሉ ይመስለኛል።
እናቴ ስትጣራ ሰማሁና እሮጨ ወደቤት ገባሁ። ቀዩ ሰውዬ እግሩን አጣምሮ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ተመለከትኩ። ጥቁር ሙሉ ሱፍ ለብሷል። ሹል ጫማው እንደመስታወት ያበራል። እናቴ ልጅ አበራ እያለች ደጋግማ ስታነሳው ሰምቻለሁ። ትልቁን ሰውዬ ለምን ልጅ አበራ እንደምትለው ይገርመኝ ነበር።
ሳሎኑ በራፍ ላይ ትንሽ ቆም ብዬ ካደፈጥኩ በኋላ ወደ ውስጥ ዘለኩ። ጋሽ አበራ በፈገግታ ተቀብሎ እየሳመኝ ስለማደጌ ይናገር ጀመር። እንዴ! እንዴ! … ጎረምሳ አይደል እንዴ? ካየሁት ብዙ ቆየሁ ማለት ነው? በጣም አድጓል …
“አዎን! ይሄውልህ ቁመቱ ተመዞ ተመዞ የት ሊደርስ እንደሆን እንጃ። ሸንበቆ መስሎልሃል። በዚህ ላይ እህል ያባቱ ገዳይ ነው። በአጥንቱ ነው የሚወዛወዝ። እንደው ምን እንደሚሻለኝ አላውቅም …” እናቴ የዘወትር ምሬቷን ጀመረች።
“ትምህርትህንስ ስንተኛ ክፍል ደረስክ?” ጋሼ አበራ ሲናገርም ሲጠይቅም በፈገግታ ነው። ትናንሽ ፍንጭት ጥርሶቹ ነጫጭና የሚያምሩ ናቸው። ዝም አልኩ፣ እኔ ስለመኪናዋ ነበር የማስበው፣ ሲወጣ ውስጥ ገብቼ ለመቀመጥ ቸኩያለሁ።
“አትናገርም እንዴ? ምን ይዘጋሃል?” እናቴ ተቆጣች።
“ከአምስተኛ ወደ ስድስተኛ አልፌአለሁ።”
“ጎሽ በርትተህ የለም እንዴ!”
ሮጨ ሄጄ ሰርተፍኬቴን አምጥቼ ሰጠሁት። እያገላበጠ ካየ በኋላ ደረጃው “ጥሩ ነው። ደህና ውጤትም ነው ያመጣው። ለመሆኑ የት ትምህርት ቤት ነው የሚጀምረው?” አያይዞ ጠየቀ።
“እንግዲህ አንዱጋ ወሽቅልኝ። ወደዚህ ወደታች ስቢስቴ የሚሉት ትምህርት ቤት አለ ሲሉ ሰምቻለሁ። ወደዛ ወደገብርኤልም መውረጃም አንድ ትምህርት ቤት አለ ይባላል። ወደ ጨርቆስም አንድ ጥሩ ትምህርት ቤት ተከፍቷል አሉ። ሲያስተምሩ ደህና ናቸውም ይላሉ።”
“የለም እዚሁ እቅርቡ አይሻለውም?” ጋሼ አበራ ስቢስቴን መረጠ። ለዳሪክተሩ የሚሰጥ አንድ ወረቀት ላይ ጻፍ ጻፍ አድርጎ ለናቴ ሰጣት።
በላብ በወረዛ እጄ ጨብጨ ለዳሪክተሩ የሰጠኋት ወረቀት ያን ያህል ክብደት እንዳላት አልተረድሁም ነበር። ፊታቸውን እንዳኮሳተሩ የተቀበሉኝን ወረቀት ሲያነቡ የቆዩት ዳሪክተር አንገታቸውን ቀና ያደረጉት የመገረምና የመደናገጥ ስሜት አዝለው ነበር። ቀጥ ብለው ቆመው ሲያዩኝ ከቆዩ በኋላ ስንተኛ ክፍል ነህ? ብለው ጠየቁኝ።
“ወደ ስድስተኛ አልፌአለሁ።”
“ሰርተፍኬት ይዘሃል?” ደብተሬን እስካገላብጥ አልጠበቁም። እጄን ይዘው በቀይ ሸክላ ወደተሰራ ህንጻ አመሩ። ኮሪደር ዘልቀው ገብተው 6ኛ ክፍሎችን በሙሉ አዳረሱ። ሁሉም ሞልተዋል። ቦታ የለም ብለው ሊመልሱኝ አልደፈሩም። አንዱን አስተማሪ ጠርተው “አንተ ክፍል ይማር።” ብለው ትዛዝ ሰጡ።
አስተማሪው ቅሬታውን መደበቅ አልቻለም። “እኔ ክፍል ምንም ቦታ የለም …”
“እንደምንም አስቀምጠው።” ዳሪክተሩ ፊታቸውን አዞሩ።
አስተማሪው ከኋላቸው ሲያቸው ከቆየ በኋላ እራሱን እየነቀነቀ “6ኛ E” ይዞኝ ገባ። እውነትም ክፍሉ በተማሪዎች ጥቅጥቅ ብሎ ሞልቷል። በአንዱ መቀመጫ ላይ ሶስት ሶስት ተማሪዎች ተቀምጠዋል። አስተማሪው ከዳር እስከዳር ክፍት ቦታ ሲቃኝ ከቆየ በኋላ የበኩሉን ትእዛዝ ሰጠ።
“ልጆች ተጠጋግታችሁ አስቀምጡት” ከትንሽ ቆይታ በኋላ አንዱ ጠራኝ። ከአንድ ሴትና ከአንድ ወንድ ልጅ ጋር በቀሪ ተማሪ ቦታ ተቀምጨ ትምህርት ጀመርኩ። የጋሼ አበራ ስልጣን ባይገባኝም በዳሪክተሩ ሁኔታ ክብር ያለው ሰው መሆኑን ተረድቻለሁ። ለመሆኑ ዶ/ር አበራ ጀምበሬ ማነው? እራሱን እንጠይቀው።

ጋሼ አበራ እራስህን እንዴት ትገልጸዋለህ? እስቲ ከልደትና ከእድገትህ ጀምርልን
ከትላቅ መወለድ እትላቅነት ቆጥ
መራመጃ ሆኖ አይችልም ሊያስቀምጥ
በርትቶ በመስራት በብዙ ልፋት ነው
እርከኑን ተሻግሮ ትላቅ የሚኮነው
ግጥም - ወለላዬ
ከቀ.ኃ.ሥ ንግግር የተወሰደ
(ትላቅ) የጃንሆይ አባባል
ከአዲስ አበባ በግምት ሀምሳ አራት ኪሎ ሜትር በምትርቅ ጨለሳ በምትባል ቀበሌ በሾኬ መንደር ነሐሴ 27/1920 ዓ.ም. ተወለድኩ። አባቴ አቶ ጀምበሬ ኑርልኝ እናቴ እማሆይ መአዛ ባሕሩ ይባላሉ። እናትና አባቴ በልጅነቴ ስለተለያዩ ከሁለቱም ጋር በመፈራረቅ መኖር ግዴታ ሆኖብኝ ነበር። በኋላም ከአያቴና ከናቴ ዘመዶች ጋር በአድአ፣ በአዲስ አበባ፣ በኮሳ በሊሙና በጅማ ከተማ ነበር እየተዘዋወርኩ ያደኩት።
አድአ አያቶቼ ዘንድ ስኖር የቀበሌውን ነዋሪዎች ባህልና ልማዳዊ ሥርዓት ለማወቅ በቅቻለሁ ከነዚህም አንዱ የገዳ ሥርዓት በመሆኑ የገዳን ሥርዓት ምንነት በሚገባ ተረድቻለሁ። በአድአ ኮሮዶቹና ጉብሎቹ ከመሬት ለሽ ብለው መሳሳምን አለአንዳች እፍረት ይፈጽሙታል። ፈረንጆች በፍቅር ወደቁ የሚሉት አገላለጽ በአድአ ይስተዋላል። መሳሳም በባህሉ በይፋ የተፈቀደ በመሆኑ የማይታፈርበት ልማድ ነው።
ጨለባ እትብቴ የተቀበረባት፣ ትኩስ ወተት እየጠጣሁ ያደኩባት፣ በእረኝነት ከከብቶች ጋር የተሯሯጥኩባት፣ ከማሳ እሸት በመሸምጠጥ፣ በሜዳ እንኩቶ በማንኮት የበላሁባት በመሆንዋ የማስታውሳት በአንክሮ ነው።
ሊሙ በቆየሁበት ዘመን የሊሙ ኮሳን፣ የሲቃንና የኖኖን ወረዳዎች ከአባቴ ጋር እየተዘዋወርኩ ለማየት ችያለሁ።በየጅማ ከተማ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች ዘመናዊ ህንጻ በብዛት የሚገኝባት የከተማዋ ቅያስም በዘመናዊ መልክ የተቀየሰላት፣ ልምላሜዋ ለዓይን የሚማርክ በረባዳ ስፍራ የተቆረቆረች፣ በተራሮች የተከበበች በመሆኗ ጉምና የማለዳ ወርጭ የማይለያት ከተማ እንዳነበረች አስታውሳለሁ።
የህይወቴን ረጅሙን ጊዜ ያሳለፍኩት በአዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ የዛሬውን አያድርገውና ወይና ደጋ የአየር ጸባይ ያላት ከተመ ነበረች። ከተማይቱ መላውን የኢትዮጵያን ጎሳዎች የሚወክሉ ሰዎች የሚኖሩባት በመሆኗ ሁሉም የእኔ ሲላት ቆይቷል። የድሀ ጎጆ ተቅልሶባትና የሀብታም ቪላ ጎን ለጎን ታንጾባት የምትታየው አዲስ አበባ በወቅቱ መደብሮቿና ሱቆቿ የተያዙት በአረቦችና በህንድ ነጋዴዎች ነበር። በኋላ በኋላ ጉራጌዎችና ትግሬዎች መጠነኛ ሱቆች እና መደብሮች በነሱው መልክ እየከፈቱ ባእዳኑን በማዳከም ንግዱን ለመቆጣጠር ችለዋል።
ከኢጣሊያ ወረራ ማግስት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደተጎናጸፈች በአዲስ አበባ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው በተመላላሽነትና በአዳሪነት ትምህርት መስጠት ጀመሩ። እኔም ቀደም ብዬ በአያቴ በደብተራ ባህሩ ወልደማሪያም ንባብና የቃል ጥናት እንዲሁም አምስቱን ሚስጥረ ቤተ ክርስቲያን ስላጠናሁ ከሌሎች የትምህርት ጓደኞቼ ብልጫ ነበረኝ። በኋላም በአዲስ አበባ በጎላ ሰፈር አለቃ ፍስሐጽዮን በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ገብቼ ዳዊት መድገምና ዜማ (ጮኩ) ተምሬአለሁ ድቁናም ተቀብያለሁ።

ዘመናዊ ትምህርትስ እንዴት ጀመርክ? “በድርሳነ ህይወቴ” መጽሐፍህ ምን ነበር ያልከን? ጋሼ አበራ ቀጥል፣
አለ በውስጣችን
እውነት ፍጹም ሆና እምታበራበት
ደግሞም ማወቅ ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
በውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ
ግጥም - ገብረክርስቶስ ደስታ
አባቴ ለስራ ወደ ጅማ ሲዛወሩ ከሊሙ ወደ ጅማ ከተማ ይዘውኝ ሄዱ። ስራቸው እንደገና ወደ አዲስ አበባ የሚያስመልሳቸው በመሆኑ እኔ ከእንጀራ እናቴ እህት ዘንድ ሆኜ ዘመናዊ ትምህርት እንድጀምር አደረጉ።
janhoy
ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዲፕሎማ ስቀበል
ከዓመት በኋላም ወደ አዲስ አበባ አምጥተውኝ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብቼ በተመላላሽነት ትምህርቴን ቀጠልኩ። ከሚሰጠኝ ትምህርት መካከል ሂሳብና አማርኛ ተሰጦዬ ስለነበር በአስተማሪዎቼ አድናቆት ነበረኝ። አልፎ አልፎም በአማርኛ የምጽፋቸው ድርሰቶች በጋዜጣ እየታተሙ ለህዝብ ይቀርቡ ነበር።
በዚህ ጊዜ መኖርያዬና ትምህርት ቤቱ ብዙ ስለሚራራቅ በእግር እየተመላለሱ መማሩ አዳጋች ቢሆንብኝም ለትምህርት ባለኝ ፍቅር ምክንያት ችግሩ ሊያሸፈኝ አልቻለም። በጣም አዳጋች በሚሆንብኝም ወቅት ወደትምህርት ቤቱ ቀረብ ያሉ ዘመዶቼ ጋ በማረፍና በመኖር ትምህርቴን ገፋሁ። የመጨረሻ ውሳኔዬ ግን እየሰራሁ የማታ ትምህርት መማር ሆነ።
ይሄንን የወሰንኩት በመንገድ ርቀት በሚደርስብኝ መጉላላት ብቻ ሳይሆን እናቴንም ለመርዳት በማሰቤ ጭምር ነበር። “ሰው ያስባል እግዚአብሔር ይፈጽማል” ነውና ስራ ለማግኘት ቻልኩ፤ በማታም እየተማርኩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በአስተዳደር ምስክር ወረቀት፤ እንደገናም ድግሪ የሚያስገኝ ትምህርት ሲጀመር በህዝብ አስተዳደር (በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን) (B.A.) ባችለር ድግሪ፣ የሕግ ፋካልቲ (የሕግ ትምህርት ቤትም) ሲከፈት የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች ጋር ትምህርቱን ተከታትዬ ኤል.ኤል.ቢ. (LLB) ድግሪ ለማግኘት በቅቻለሁ።

ህዝባዊ አገልግሎትህስ እንዴት ነበር? የት መስሪያ ቤት ነበር ሥራ የጀመርከው?
ለመሰሏ ልትጥር ለሌላው ልትሰራ
ለመጪው ልታቅድ ምኞት ልታደራ
ነፍስ አላት ተልዕኮ አለባት አደራ
ግጥም - ዓለምፀሐይ ወዳጆ
ለመጀመሪያ ጊዜ በንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ጽ/ቤት በመዝገብ ቤት ሰራተኛነት ተቀጠርኩ። ስራው እጅግ ብዙ ነበር። ከተሰጠኝ መደበኛ ስራ ውጪ ስራው ደብዳቤ መጻጻፍ፣ ንግግሮችን መተርጎም፣ ከረጅም ደብዳቤዎች ፍሬ ነገሮችን መልቀም፣ ከሀገርና ከመንግስት መሪዎች የሚደረጉ መጻጻፎችን በቅርብ መከታተልን የሚያጠቃልል በመሆኑ ለጋው አእምሮዬን በዕውቀትና በስራ ልምምድ ለማጎልበት ረድቶኛል።
በተጨማሪ በብርቱ ጥንቃቄ የሚያዙ ሚስጥርነት ያላቸው ጽሁፎች፣ ከፍተኛ አማካሪዎች የሚአቀርቧቸው የጥናት ጽሁፎችና ሪፖርቶች በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉበት ቦታ ማኖሬም የማስታወስ ችሎታዬን ከፍ አድርጎታል።
በዚሁ መስሪያ ቤት ብዙ ልምድ ካገኘሁ በኋላ በወጣቶች ድርጅት ውስጥ ለመስራት ፍላጎት ስላደረብኝ የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር ሲቋቋም የማኅበር የስራ ፈጻሚ ፀሐፊ በመሆንም እንድሰራ ተዛወርኩ። በዚህ ማኅበር ስራ ላይ ለረጅም ጊዜ የቆየሁ ሲሆን፤ ወጣቶቹ ለሃገራቸው የሚበጁ፣ ለወገኖቻቸው የሚጠቅሙ በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጹ፣ እንዲሆኑ ጥረት አድርጌያለሁ።
በመካከሉ በውጪ ሐገር የስራ ጉብኝት አድርጌ ስመለስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጽ/ቤት ቤት ዋና ፀሐፊ ሆኜ ተሾምኩ። በጊዜው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ባስሊዮስና በእንደራሴው በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የበላይ ተቆጣጣሪነት፣ ሌላ ሥራ አስኪያጅ ከበላዬ ሳይኖር ከሶስት ዓመት በላይ በኃላፊነት ቆይቻለሁ።
papas
በዌስት ኢንዲስ
ይህ መስሪያ ቤት በስራው ብዛትና ስፋት ከመንግስት ጠቅላላ አስተዳደር የሚያንስ ቢሆንም በብዙ ረገድ መንግስት ካለው አቋምና የስራ መስክ ጋር ተመሳሳይነት አለው። የትምህርት፣ የባህል፣ የጥንታዊ ቅርስ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ዳኝነት የግብር አሰባሰብ፣ የህብረት ሥራ፣ የውጪ ግንኙነት፣ የስብከትና የማኅበራዊ አገልግሎት፣ ስራዎች አጠቃሎ የያዘ ነው።
በመሆኑም ለስራው አመቺነት ድርጅታዊ ሰሌዳ (ቻርት)፣ የስራ አከፋፈል ዝርዝርና የውስጥ ደንብ አውጥቼ በስራ ላይ እንዲውል አደረኩ። የወጣውም የውስጥ ደንብ ለሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤቶችም ጭምር ስለሆነ ሁሉም የኃላፊነቱን መጠንና ገደብ አውቆ ለመስራት ችሎ ነበር።
ሌላው በወቅቱ የንጉሠ ነገሥቱ የብር እዮቤልዩ ይከበር ስለነበር በክብረ በአሉ ቦታ ላይ ጥንታዊ የታሪክ ቅርሶችን ከየአድባራቱና ገዳማቱ በማስመጣት ለኢትዮጵያውያንና ለውጪ ሀገር ጎብኝዎች በትርኢት መልክ እንዲታይ አድርጌአለሁ።
የትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በዘመናዊ የህትመት መሳሪያዎች እንዲደራጅ በማድረግ በወቅቱ አስፈላጊ የሆኑ መጻሕፍት በብዛት እንዲታተሙ መንገድ ከፍቻለሁ። ከሁሉ የማይረሳኝና ትዝ የሚለኝ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ቅድስት ማርያም ደብር አካባቢ የነበራት ሰፊ የከተማ ቦታ የባለርስትነት መረጃ (ካርታ) ስለጠፋባት ቦታው በግለሰቦች እጅ በእጀ መናኛ ተይዞ ቆየቶ ነበር።
ይህ ሁኔታ ስላሳሰበኝ የቤተ ክህነቱ ሀብት በከንቱ መቅረቱም ስላስቆጨኝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በመመካከርና በማፈላለግ በብዙ ልፋትና ድካም ካርታው ለማግኘት ቻልኩ። ከዚያም በቦታው ላይ ለቤተክርስቲያን ቋሚ ገቢ የሚያስገኙ ሁለት ትላልቅ ህንጻዎች ሊሰሩ ችለዋል። በዚህም ምክንያት የንጉሠ ነገሥቱን ምስጋና፣ የብጹህ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን ቡራኬና ምርቃት ለማግኘት በቃሁ።
ብልሃትን፣ ታዛዥነትን፣ ቅንነትና ከሰው ጋር መግባባትን እንዲሁም ዘዴና ትዕግስትን በሚጠይቀው በዚህ የቤተክህነት ስራዬና በተለይም ንብረትን ለማስመለስ ያደረኩት ጥረት በንጉሡ ሞገስ እንዳገኝ ስላደረገኝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ምክትል አስተዳዳሪና የቤተ ሰይዳ ሆስፒታል ኃላፊ ተደርጌ ተሾምኩ።
በዚሁ ስራ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየሁ በኋላ ደግሞ የሚንስትሮች ምከር ቤት ዋና ፀሐፊ ሆኔ ተሾምኩ። ይህንን ከፍተኛ የኃላፊነት ስልጣን ያሰጠኝ ንጉሠ ነገሥቱ በዌስት ኢንዲስ ጉብኝት አድርገው ሲመለሱ ቀደም ብዬ በስፍራው ተገኝቼ እዛ ለተቋቋሙት ቤተ ክርስቲያናት በቂ በጀት እንዲሰጥ ያዘጋጀሁትን ቃለ ጉባኤ እንዲሁም ካይሮ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው የአፍሪካና የእስያ ህዝቦች አንድነት ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያ መልክተኞች መካከል አንዱ ሆኜ ስመለስ ያቀረብኩት ሪፖርት በመመከታቸው ይሆናል የሚል ግምት ወስጃለሁ።
meeting
በውጪ ሐገር ስብሰባ ላይ
በዚህም የስራ መደብ ለአንድ ዓመት ከቆየሁ በኋላ እንደገና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ተጠባባቂ ሹም ሆኜ ተመለስኩ። ቀደም ሲል ይሄንኑ ድርጅት በምመራበት ወቅት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሆስፒታል፣ የብርሃንና ሰላምን ማተሚያ ቤት፣ የብርሃን የጽህፈት መሳሪያ መደብር፣ በእኔ ሀላፊነት ስር እንዲሆኑ ተደርጎ ስለነበረ፤ እሱንም በመደረብ በኃላፊነት ሰርቻለሁ። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እንዲስፋፋ ጥናት አቅርቤ በጥናቱ መሰረት ሊሰራ ችሏል።
በ1953 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎ ከከሸፈ በኋላ የመንግስት አቋም በአዲስ መልክ እንዲደራጅ የሚንስትሮች ምክር ቤት የበለጠ ስልጣን እንዲኖረው ስለተፈለገ የጽህፈት ሥራ አመራር ልምድ ያለኝና በተለይም በቦታው ላይ በፊት የሰራሁ መሆኔ ስለሚታውቅ በድጋሚ የሚንስትሮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊቱን ስልጣን ያዝኩ።
በዚሁ ሹመት ለአስር አመት የሰራሁ ሲሆን የስድስቱን ዓመት በምክትል ሚንስትር ማዕረግ ካገለገልኩ በኋላ በ1963 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በጠቅላይ ምኒስቴር ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሆኔ ተሾምኩ። የተሰጠኝም የስራ ድርሻ የሕግና የፓርላማ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊነት ነበር ይህ የሥራ መደብ እጅግ ሰፊ ስራ የሚያጠቃልል ሲሆን፤ የጠቅላይ ሚንስትሩንም ሥራ የሚጋራ ነበር።
በፓርላማ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቋሚ ተወካይ በመሆኔ በመንግስት ስም ለሚቀርቡት የሕግና የስራ አፈጻጸም ጥያቄዎች መልስ መስጠትና ለፓርላማ የሚቀርቡ ሕጎችን መንፈስ፣ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ለፓርላማው ማስረዳት አንዱ የሥራ ድርሻዬ ነበር።
በዚህም መሰረት ፀሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን እና ልጅ ሚካኤል እምሩን በመወከል በሕግ መወሰኛና በሕግ መምሪያ ምክር ቤቶች የመንግስት ተጠሪ ሆኜ ፓርላሜንቱ እስከተበተነበት ጊዜ ድረስ ሥሰራ ቆይቻላሁ።

ስለ ጎጆ መውጣህ አላጫወትከንም እኮ፤ የትዳር ህይወትህ እንዴት ነበር?
አዳም የትናንቱ
የጥንት የጠዋቱ
ሳይለፋ ሳይታክት ተኝቶ ባደረ
ውኃ አጣጭ አቻውን ከጎኑ ተቸረ
ይብላኝ ላሁኑ አዳም ለታካች ሚስኪኑ
ምነው በተኛበት በሸሸሁ ከጎኑ
ለምትል ሄዋኑ
ግጥም - በዕውቀቱ ስዩም
with wife
ከባለቤቴ ከወ/ሮ ንግሥት ጋር
ሥራ ከያዝኩ በኋላ ለጥቂት አመታት ከአባቴና ከእንጀራ እናቴ ጋር ደጃች ውቤ በሚባለው ሰፈር እኖር ነበር። ቀጥሎ ወደ ጎጆ ምስረታ ተሻግሬ ወይዘሮ ንግሥት ዘውዱን አገባሁ። የተጋባነው በኪራይ ቤት ነበር፤ እያደር የራሳችንን ቤት አቅማችን በፈቀደው ያህል መስራት ቻልን። በፍቅር የተገነባ ቤታችን ልጅ እሚጮህበት ባለመሆኑ ደስታችንን አደብዝዞት ቢቆይም ብዙ ከዘገየን በኋላ ሁለት ወንድ ልጆች ለማፍራት ችለናል።
የመጀመሪያው ልጅ እንደተወለደ ለጥቂት አመታት ያህል ፍቅራችን እንደገና አብቦ እኔም በስልጣን ላይ ስልጣን በክብር ላይ ክብር ደርቤ ከልጅ ሲሳይ ጋር በሰላም ከረምን። ውሎ ሳያድር የ1966 ዓ.ም.ቱ የለውጥ ማዕበል መጣ። ማዕበሉ እየገፈተረ፣ እያላጋ ከጣላቸው መካከል እኔንም አንዱ ስላረገኝ የትዳር ህይወቴ እንደነበረ ሊዘልቅ አልቻለም። ክፉ እጣ! …
“ደርሳነ ህይወቴ” መጽሐፍህ ስለ ማኅበራዊ አገልግሎትህ ምን አስፍሯል? ቀንጨብ አድርገህ ብትነግረን፤
የማይነጋ ሕልም ሳልም
የማይድን በሽታ ሳክም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የሰው ሕይወት ስከረክም
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም
ግጥም - ሎሬት ፀጋዬ /መድኅን
በቅድሚያ የምገልጸው የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበርን (ወ.ወ.ክ.ማ) ነው። ከማኅበሩ ምስረታ ጀምሮ ለአስራ ዘጠኝ አመታት ያህል አገልግያለሁ። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአባልነት በቦርድ አባልነት፣ በክብር ዋና ፀሐፊነት በመጨረሻም በምክትል ፕሬዝደንትነት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደግሞ በልማት ኮሚሽን በአባልነት፣ በአስተዳደር የቦርድ አባልነት በተራድኦና የስደተኞች ኮሚቴ በአባልነት፣ የአገልግሎት ደርሻዬን አበርክቻለሁ።
በድኩማን ረዲኤት ድርጅት፣ የሲሽየር ቤት በሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት በቦርድ አባልነት በስጋ ደዌ ህሙማን መርጃ ማኅበር፣ በኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር፣ መጻፍና ማንበብ የማይችሉን ማስተማር እንዲቻል በተመሰረተው በኢትዮጵያ ፊደል ሰራዊት ማኅበር፣ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በቦርድ አባልነት፣ በሊቀ መንበርነትና በምክትል ሊቀ መንበርነት ሰርቻለሁ።
ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ዘመናት ለረጅምና ለአጭር ጊዜ በሕግ መምሪያ ምክር ቤት መማክርት ምርጫ ቦርድ፣ የገንዘብ ቁጠባና በመኖርያ ቤት ሥራ የህዝብ ማኅበር፣ በብሄራዊ ሀብት ልማት አክሲዮን ማኅበር፣ በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር፣ በግዮን ሆቴል አክሲዮን ማኅበር፣ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አክሲዮን ማኅበር፣ በተሽከርካሪ መኪናዎች አክሲዮን ማኅበር፣ በተዋህዶ ጥበብ ፋብሪካና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ዩኒስኮ፣ (የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት) ኮሚሽን በቦርድ አባልነት በሌሎቹም ቦታዎች እንደዚሁ በሊቀ መንበርነትና በቦርድ አባልነት አገልግያለሁ።
ይህን ማኅበራዊ አገልግሎቴን እንደመደበኛ ስራ ከዋና ስራዬ ጋር በመደረብ ብሰራም ደምወዝ የሚከፈልበት አልነበረም፤ ነገር ግን በየጊዜው ለስራ አገልግሎቴ የወርቅ መዳሊያና የገንዘብ ሽልማት አግኝቻለሁ። ከሁሉም በልጦ የሚያስደስተኝ ግን በበጎ ስራ አገልግሎቴ የማተርፈው እርካታ ነበር።
የውጪ ሀገር ተልኮህስ እንዴት ነበር? ወደ የትኞቹ ሀገሮች ሄደሃል? በምን በምን ጉዳይ?
አቀበቱን ወጣሁ ቁልቁለቱን ወረድኩ
ሲልኩኝ ተልኬ ሲጠሩኝም ደረስኩ
ለጭቁን የቆሙት ይሄን ሰምተውብኝ
ሳልደክም ደክመሃል ብለው አሳረፉኝ
ግጥም - ወለላዬ
የመጀመሪያ ጉዞዬ አሜሪካና ዌስት ኢንዲስ በባህልና በኃይማኖት መልክተኝነት ነበር። በዚህ ጉዞ ጅቡቲን የፈረንሳይ ግዛት የሆነችው ማርሴይ ወደብን፣ ፓሪስን፣ ለንደንን፣ ኒውዮርክን፣ ኒውጀርሲን፣ ዋሽንግተንና ከአሜሪካም ውጪ የትሪኒዳድና ቶቤጎ ደሴቶችን፣ ብርቲሽ ጊያና የተባለ ግዛትን ጎብኝቻለሁ። በየሀገራቱ የሄድኩበትንም ተልእኮ ፈጽሜአለሁ። ስለዚህ ተልዕኮ “ኢትዮጵያ ሀገረ ተስፋ” በሚል ርዕስ የጻፍኩት መጽሐፍ በይበልጥ ያስረዳል።
ሁለተኛውም ጉዞዬ እንደዚሁ መንፈሳዊ ጸባይ ያለው ሲሆን፤ የተጓዝኩትም ወደ ግብጽ ነበር። የግብጽ (ኮፕቲክ) ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኃይማኖት መሪዎች የኢትዮጵያን መንፈሳዊ አባት ሿሚዎች ሆነው ኖረዋል። በመጨረሻዎቹ ጥቂት ዘመናት ግን በመንበረ ማርቆስ ለሚሾመው ፓትርያርክ ምርጫ የኢትዮጵያ ካህናትና ምዕምናን ተወካዮች ተካፋይ ሆነው ይመርጡ ነበር። ግብጻውያኑ ይሄን እያወቁ ብቻቸውን የተመረጡትን ጳጳስ በማውረዳቸው በኢትዮጵያ መንግስት ቅሬታ አሳደረ።
በዚህ ምክንያት የአሰራሩን መዛባት ለማስረዳትና ለወደፊቱም ሊደረግ የሚገባውን ተነጋግሮ ለመስማማት በማስፈለጉ ይህን ማስፈጸም አንዱ ተልኮዬ ነበር። ሁለተኛው ተልኮዬ ደግሞ (አፍሮኤሽያን ፒፕልስ ሶሊዳሪቲ ኮንፍራንስ) ለመካፈል ከአፍሪካና ከእስያ ከመጡት መልክተኞች መካከል የኢትዮጵያ መልክተኛ በመሆን ነበር።
ሌላው ዋናው መስሪያ ቤቱ ጄኔቫ የሆነው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማኅበራትን በሚያስተባብረው (ሊግ ኦፍ ሬድ ክሮስ ኤንድ ሬድ ክሬስንት ሶሳይቲስ) በሚለው ድርጅት ቀይ መስቀልን ወክዬ በተደጋጋሚ በጀኔቫ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቻለሁ። በሜክሲኮና በቴህራንም የሉካንን ቡድን በመምራት ሄጃለሁ።
red cross
በቀይ መስቀል ማኅበር ስብሰባ
የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበርን (ወ.ወ.ክ.ማ) በመወከል ደግሞ ኡጋንዳ ካምፓላ፤ የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበርን በመወከል በናይሮቢ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርን በመወከል በዩጎዝላቢያ ተገኝቻለሁ። በኦስትርያ ቪየና በዓለም ትራንስፖርት ስብሰባ ኢትዮጵያን በመወከል፣ ብጽዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዓይናቸውን ታመው እሳቸውን ለማሳከም ስዊድንና እስራኤል ሄጃለሁ።
በተጨማሪም ለብሄራዊ ፊደል ሰራዊት መርጃ ገንዘብ ለማሰባሰብ በአሜሪካ በቦስተን ከተማ የሄድኩ ሲሆን፤ በጠቅላላው በልዩ ልዩ ተልዕኮና እግረ መንገዴንም ከጠቀስኳቸው ውጪ ኩባን፣ ግሪክን፣ ጆርጅያን፣ ኢራንን፣ ሊባኖስን፣ ቱርክን፣ ሜክሲኮን፣ ስዊዘርላንድን፣ ዩጎዝላቪያን፣ ሃንጋሪን፣ ችኮዝላቫኪያን፣ ሩማንያን፣ ራሽያን፣ ኦስትርያን፣ ህንድን፣ ጃፓንን፣ ዴንማርክን፣ ፊላንድን፣ ኖርዌይን፣ ኢጣልያን፣ ምዕራብና ምስራቅ ጀርመንን፣ ስፔንን፣ ሆላንድን፣ ኬንያን፣ ዩጋንዳን፣ ሴኒጋልን፣ ጋናን፣ ቤልጅግን፣ ሎክሰበርግንና ካናዳን የመጎብኘት እድል አግኝቻለሁ።

ጋሼ አበራ ለዚህ ሁሉ አገልግሎቱ መንከራተቱና ሩጫው ያተረፈው እስራት ነበር። ለምን ለውጥ መጣ። ማንንም ከማን አለየም። እከሌ ምን ሰራ እከሌ ምን አጠፋ የለም። “እሰረው! ያዘው! ግደለው!” ብቻ ሆነ ማን ተረፈ ከባለስልጣን እስከ ተራ ሰራተኛ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አለቀ። ከዳር እስከ ዳር ሽብር ከዳር እስከ ዳር እስር ሆነ። ጋሼ አበራም የለውጡ አፍ ማሟሻ ከሆኑት ባለስልጣኖች አንዱ ሆኖ ለስምንት ዓመታት ያህል በእስር ቆየ። ስለ እስራቱ ለምን እራሱን አንጠይቀውም …
ጋሽ አበራ ለምን ታሰርክ? እስራቱስ እንዴት ነበር?
እግዜር ደግነቱ
ቆንጆ አርጎ መስራቱ
የአምላክ መጥፎነቱ
ፍጡሩን ማጥፋቱ
አብዮት እግዜር ነው ከግዜርም
ይበልጣል
እንደ ጭራቅ ድመት ልጆቹን
ይውጣል
ግጥም - አበረ አዳሙ
መስከረም 27 ቀን 1967 ዓ.ም. ነበር የታሰርኩት። ወደ ሌላ ቢሮ ወጥቼ ወደራሴ ቢሮ ለመመለስ ደረጃው ላይ እንዳለሁ ሁለት የማላውቃቸው ሲቪል የለበሱ ሰዎች፣ “አቶ አበራ ጀምበሬ እርስዎ ነዎት?” ሲሉ ጠየቁኝ መሆኔን አረጋገጥኩ፤ አልዘገዩም ለስራ ጉዳይ ወደአራተኛ ክፍለ ጦር እንደምፈለግ ነገሩኝ፤ አያይዘውም “እንሂድ!” በማለት በትዕዛዝ መልክ ጥያቄ አቀረቡ፤ ምን ማድረግ እንደምችል አላውኩም፤ ጉዞ ጀመርኩ። ከትንሽ እርምጃ በኋላ ግን ማስታወሻ ለመያዝ ወደቢሮ ለመመልስ እችል እንደሆን ጥያቄ አቀረብኩ፤ የተሰጠኝ መልስ “አሁኑኑ ስለሚመለሱ በቀጥታ እንሂድ!” የሚል ነበር።
የተረፈችኝ አንድ ጥያቄ በራሴ መኪና ልከተላችሁ የምትል ነበረች “የለም! እራሳችን ስለምንመልስዎት መኪና መያዝ አያስፈልግዎትም” የሚል አጭር መልስ ተሰጠኝ። ከዚህ በኋላ ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር አመራን እንደገባን ሻለቃ ዳንኤል አስፋው የሚባል ተቀበሎኝ፤ ማህደር አውጥቶ ውስጡ የሰፈረውን ከቃኘ በኋላ በቁጥጥር ስር እንድቆይ መታዘዙን ነገረኝ።
ሻንበል ጥበበ ሙለታ ተረክቦኝ በሰባት ቁጥር የእስር ክፍል ከወሰደኝ በኋላ ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅዬ የእስራት ጊዜዬን አንድ ብዬ መቁጠር ጀመርኩ። እስከ ጥቅምት አጋማሽ ከቆየሁ በኋላም ወደ ታላቁ ቤተ መንግስት ለረጅም ጊዜ እስራት ተዛወርኩ።
በዚሁ የእስር ስፍራ ከሰማንያ አንድ ባለስልጣኖች ጋር ከምድር በታች በተሰራ አዳራሽ ውስጥ እጅግ አስጨናቂ በሆነ ሁኔታ ቆየሁ። በስምንት ዓመት የእስር ቆይታዬ ወቅት አያሌ ችግሮች ደርሰውብናል። ያንን “የስር ቤቱ አበሳ በታላቁ ቤተ መንግስት” በሚል ርዕስ በጻፍኩትና ለንባባብ ባበቃሁት መጽሐፌ በዝርዝር ገልጨዋለሁ።
drsaneሆኖም በመጠኑ ለማንሳት በዚህ የእስራት ቦታ ከገባሁ አንድ ወር በኋላ ከመካከላችን አርባ ሰባት ባለስልጣኖች ተለቅመው ከሌሎችም የእስር ቦታዎችና ሆስፒታልም የነበሩ ሳይቀሩ እንዲመጡ ተደርገው ስልሳ ባለስልጣኖች ተገደሉ። ይህን እንድንሰማ በጋዜጣም ከወጣ በኋላ እንድናነብ ተደረገ።
በየጊዜው ከመካከላችን እየተወሰዱ አድራሻቸው የጠፉም ነበሩ። ብፁህ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ፣ አቶ ሰይፉ ማህተመ ሥላሴ … እና ሌሎቹም ታንቀው መገደላቸውን በኋላ ለመስማት ችለናል። በቀዝቃዛ ወለል ላይ ለረጅም ጊዜ እንድናድር ተደርጓል። ለቤተሰባችን ይሰጥ የነበረው አንድ መቶ ሀያ ብር እንዲቀር ተደርጎ ሳሙናና ሶፍት ማቅረቢያ ያጣ ቤተሰብም ነበረ።
ከቤተሰብ ጋር መተያየት የሚቻለው ለዋና ዋና በዓሎች ብቻ ነበር። ያም በረጅም እርቀት ቆሞ ከመጯጯህ በስተቀር ተቀራርቦ መነጋገር ስለማይቻል ትርፉ መሳቀቅ ነበር። በጠቅላላው ህይወታችን ዋስትና ስለሌለው ኑዛዜ ጽፈን ለቤተሰቦቻችን ሰጥተን ነበር።
ያም ሆኖ በዚህ የእስራት ዘመን ምንም እንኳን በማይመች አቀማመጥ ስጽፍ ሰውነቴ ቢጎዳም በተለይም የተፈጥሮ ብርሃን በሌለበትና በሰው ሰራሽ ደካማ ብርሃን ዓይኖቼ ቢጎዱም መጻሕፍትን በመተርጎም፣ የምርምር መጻሕፍትን፣ ያገራችንን ትላልቅ ጀግኖች ታሪክ እና ሌሎችንም መጻሕፍት ለመጻፍ ችያለሁ። ከጻፍኳቸውም መካከል፤
• የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ታሪክ (አባኮስትር በላይ ዘለቀ) ተብሎ የታተመ
• የድርሳነ ህይወቴ ረቂቅ በዚሁ ርዕስ የታተመ
• ስለታላቁ ቤተ መንግስት የእስራት ህይወት (የእስር ቤቱ አበሳ በታላቁ ቤተ መንግስት)
በሚል የታተመ
• የራስ አበበ አረጋይን ብሄራዊ ጀግንነት የሚገልጽ (አባ ገስጥ ራስ አበበ አረጋይ) በሚል የታተመ
• ስለ ፀሐፊ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ ታሪክ (ብቸኛው ሰው) በሚል የታተመ
• የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት በተመለከተ የትርጉም ሥራ (የኢትዮጵያና ኢጣሊያ የ1928 ዓ.ም. የማዕከለ-ሐወርት (ኢንተርናሽናል) ጉዳዮች በሚል የታተመ
• የሕግ ሊቃውንት የጻፏቸው የምርምር ስራዎች ትርጉም
እነዚህ እስር ቤት የተጻፉና ከኔው ጋር ከእስር የወጡ ናቸው።

ከእስር እንዴት ተፈታህ? ከእስር በኋላ ህይወት እንዴት ነበር?
ያደናቅፋሉ በማለት ጠርጥሮ
አለጥፋታቸው ስምንት ዓመት አስሮ
ቄንጠኛው አያ ደርግ የዛን ጊዜው ጌታ
ባለስልጣናቱን ማርኩኝ ብሎ ፈታ
ግጥም - ወለላዬ
መስከረም 1 ቀን 1975 ዓ.ም. ደርግ ስልጣን ከያዘ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘመን መለወጫ ቀን እንደታምር በሚቆጠር ሁኔታ ሰባት መቶ አስራ ስድስት የፖለቲካ እስረኞችን በምህረት መፍታቱን ገልጾ ለቀቀ። ከነዚህ ተፈችዎች መካከል አንዱ እኔ ሆኜ ተገኘሁ።
ስምንት ዓመታት ወደቆየሁበት እስራት የገባሁት አለጥፋቴ በድንገት እንደሆነ ሁሉ ስፈታም እንደዚሁ ባላሰብኩት ጊዜ በድንገት ነበር። ስፈታ የተሰጠኝ ወረቀት ላይ በምህረት እንደተለቅኩ ይገልጻል።”አብዮቱን ያደናቅፋሉ በሚል ጠጥረን አስርን” የሚል ቃል ጽፈው የራሳቸውን ጥርጣሬ እኔ እንዳጠፋሁ ቆጥረው ምህረት ማለታቸው አስደናቂ አባባል ሆኖብኝ ከርሟል። ሆኖም ይህ የእግዚአብሔር ምህረት ነው ከማለት ውጪ የማደርገው አልነበረም።
ቀዝቅዞና የመከራ ጭጋግ ሸፍኖት ወደ ነበረው መኖሪያ ቤቴ ስደርስ ልጆቼ አድገው፣ ባለቤቴም ምንም እንኳን ብቻዋን ልጆች ይዛ ያሳለፈችው ዘመን ከባድ ሆኖባት እንደቆየ ብረዳም፣ ጤንነቷና ሁኔታዋ ደህና ሆኖ ስለጠበቀኝ በህይወት የመኖር ተስፋዬ በራ።
ሆኖም የፖለቲካ እስረኝነቴ ባስከተለው መራራቅ ሳቢያ ከባለቤቴ ጋር አለመስማማት በመፍጠራችን ሕይወቴ እንደገና የሀዘን ደመና አንዣበበበት። ሁኔታውም ከቀን ወደቀን እየባሰበት በመሄዱ መለያየት ደረጃ ደረስን። ነገር ግን ልጆች በመሃላችን በመኖራቸው ምክንያት የኑሮ ገመዳችንን ፍጽሞ ልንቆርጠው ባለመቻላችን ከአንዴም ሁለቴ እርቅ በመፍጠር አብሮ የመኖር ሙከራ አደረግን።
“ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ” ሆነና መለያየታችን እውን ሆኖ ሕጋዊ ጋብቻችንን አፈረስን። ባለቤቴን ምንም እንኳን በዚህ አይነት ሁኔታ ብለያትም በእስራቴ ጊዜ ያደረገችልኝ ውለታን ባለመዘንጋት በተለይም ከእስራቴ በፊት ያሳለፍነውን እረጅም የመተሳሰብና የፍቅር አመታት በማሰብ የወንድምና የእህት ያህል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ጥሬያለሁ። ልጆቻችንም በመካከላችን ስላሉ በህይወት እስካለን ድረስ የሚያስተሳስሩን ሀረጎች ናቸው።

ጋሼ አበራ ተስፋ አልቆረጠም። አሁንም የመኖርና የመስራት ፍላጎት አለው። የት ይሆን? የስራ እድል አግኝቼ ለመስራት የምችለው? እያለ ማሰቡ ግን አልቀረም። ይሄን በማሰላሰል ብዙ ሳይቆይ በስራ ላይ ስራ ተደራርቦ ነበር የገጠመው። ያውም ከሹመት ጋር እራሱ ይንገረን።
ከእስር በኋላ የስራ ህይወትህ እንዴት ነበር?
የኔ ነፃ ፈቃድ
ምን ኩሬ ቢመስልም
የረጋ ከጉድጓድ
ድንገት ቢወርድበት
ደራሽ ውኃ ኾኖ
የሌሎች ተጽዕኖ
ኃይልና ማዕረግ
ሳይፈልግ ይጓዛል
በማይወደው ፈለግ
ግጥም - በዕውቀቱ ስዩም
ከእስር ከወጣሁ በኋላ እንደገና ወደ ሥራ መግባት እንደፈራሁት አልከበደም። ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ውስጥ ብዙ በመስራቴና በእስራቴ ዋዜማም የዓለም ቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማኅበራት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እስከመሆን ደርሼ ስለነበር፤ ከተፈታሁ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለመቀጠር በቃሁ።
በቀይ መስቀል ስራ ትንሽ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ ከሚንስትሮች ምክር ቤት በተላለፈ ትዕዛዝ በሕግና ፍትህ ሚኒስቴር ተመድቤ እንድሰራ መታዘዙ ተነገረኝ። ነገር ግን በቀይ መስቀል ማኅበር መስራቴ ለኔ ዋስትና የሚሰጠኝ መሆኑን በማመን ወደ ተመደብኩበት መስሪያ ቤት ላለመሄድ ጥረት ባደርግም የሚያናግሩኝ ባለስልጣኖች የሚያውቁኝና ለኔ የሚያስቡ ችግሬንም የሚረዱ በመሆናቸው ምክራቸውን በማካፈል የሚስማማኝን የስራ ምድብ ስላመቻቹልኝ በሚንስቴሩ መስሪያ ቤት ስራ ጀመርኩ።
ስራውን በወቅቱ ከነበሩት ሚኒስትር ጋር አብሬ እየሰራሁ እያለሁ እሳቸው የብሔራዊ ሸንጎ ምስረታ ቅድመ ዝግጅት የሚያደራጅ አካል የበላይ ሆነው ወደ ደርግ ሊቀ መንበር ጽህፈት ቤት ሲዛወሩ፤ በተተኪነት ከመጡት ሚኒስትር ጋር ስራዬን ቀጠልኩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ በውጪ ሀገራት ለስብሰባና ለልዩ ልዩ ተልዕኮ እየሄድኩ እሰራ ነበር።
በመቀጠል የገጠመኝ አስገራሚ ነገር እኔ ከእስር የተፈታሁ በዚህ ላይ የኢሰፓ አባልም ያልሆኩ ስሆን፤ ለብሄራዊ ሸንጎ ምርጫ መቅረቤ ነበር። ይህ አቅርቦት ሌሎችንም ሰዎች እንደሚያሳትፍና ሁሉም ነገር በህዝብ ምርጫ እንደሚከናወን ለማስመሰል ይሆናል የሚል ግምት ይዤ ቆየሁ።
ነገር ግን ምርጫው እየተጣራ ሄዶ ካለሁበትና ከተወዳደርኩበት ወረዳ ሶስት እጩዎች ብቻ ቀረን። ከነዛ እጩዎች ደግሞ እኔ በከፍተኛ ድምጽ እንደተመረጥኩ በሬድዮ ሰማሁ። በዚህም መሰረት ብሔራዊ ሸንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰበሰብ ለምርጫ ክልሌ የተመደበውን ወንበር ያዝኩ። ስብሰባው በተከፈተ ሶስተኛም ቀን በምክትል ሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ምክር ቤት የጉባኤ ፕሮቶኮልና የፕሬስ ሀላፊ ሆኜ መሾሜን የሚገልጽ በፕሬዝዳንቱ የተፈረመ ደብዳቤ ደረሰኝ።
speech
ቡዳፔስት
በዚህ ስራ መደብ ላይ እያለሁ የመንግስት ምክር ቤት ጸሐፊ የነበሩት የምድር ጦር ዋና አዛዥ ሆነው ሲሾሙ፣ በሳቸው እግር ተተክቼ የምክር ቤቱን ፀሐፊነት ስራ በተጠባባቂነት እንድሰራ ተደረገ።
በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሸንጎ ከዓለም ፓርላማዎች ህብረት ተመልሶ እንዲገባ በመደረጉ ህብረቱ በየስድስት ወሩ በሚያደርገው ስብሰባ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ከመጡ ተሰብሳቢዎች ጋር ኢትዮጵያን በመወከል ተገኝቻለሁ። በዓለም ሸንጎ ፀሐፊዎች ስብሰባም ላይ ለመካፈል ችያለሁ።
ሸንጎው በተመሰረተ ሶስተኛ ዓመት ኢህአዴግ በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ስልጣን ሲይዝ ስራው በሽግግር መንግስት የተወካዮች ምክር ቤት እንዲካሄድ በመደረጉ የመንግስት ምክር ቤት ሰራተኞች በምኒስትሮች ምክር ቤት ስር ሆኑ። እኔም ለጥቂት ወራት እዛው ከቆየሁ በኋላ በመስከረም ወር 1984 ዓ.ም. በጡረታ ተገለልኩ።
ከዚያም ወደ ቀይ መስቀል ማኅበር እንደገና በመመለስ ለአራት አመታት ያህል አገልግያለሁ። በዚሁ ማኅበር ለረጅም ዓመት በሐገርና በውጪ ሐገር ላደረኩት የስራ አስተዋጽዖ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳይ ከማኅበሩ ተሸልሚያለሁ። ከዚህም ሌላ በ.ወ.ወ.ክ.ማ ምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ በህጻናት እርዳታ ድርጅት በአማካሪ ኮሚቴ አባልነት፣ በኋላም በበጎ ፈቃድ ሊቀ መንበርነት የሰራሁ ሲሆን፤ እድሜ የመማርን ፍላጎት እንደማይገታው በማመን ያለኝን ትምህርት የላቀ ለማድረግ ችያለሁ።

እንዴት ለላቀ ትምህርት ደረስክ?
ይኸው ነው፣ ትርፋችን ይሄው ነው እጣችን
ሕይወትን፣ ስንፈልግ፣ ሕይወት ማጣታችን
ግጥም - አበራ ለማ
ከተፈታሁ በኋላ ከመንግስት ስራ ጎን ለጎን በከፊል ግዜ በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በሕግ ፋከልቲ በመምህርነት ተቀጥሬ እሰራ ነበር። የቅጥር የአካዳሚክ ማዕረጌ “ሌክቸለር” ሲሆን፤ በኋላ ግን በረዳት ፕሮፌሰር ደረጃ አድጓል።
በዚህ የዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ወቅት ሮተርዳም ለሚገኘው ለራስማስ ዩኒቨርስቲና በላይደን ለሚገኘው የአፍሪካ ጥናት ማዕከል “የስኮላርሽፕ” የእርዳታ ጥያቄ አቅርቤ ስለተፈቀደልኝ ለስድስት ወራት ሆላንድ በመቆየት እስር ቤት ሆኜ የጻፍኳቸውን የሕግ መጻሕፍት በማዳበርና ሌሎችንም ጽሁፎቼን በማቅረቤ በዩኒቨርስቲው ተቀባይነት ስላገኘሁ በዩኒቨርሲቲው ሊቃውንት ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ተጠይቄ ተገቢ መልስ ሰጠሁ። ይህም በመሆኑ የዶክትሬት ድግሪ ከዩኒቨርሲቲው ለማግኘት ቻልኩ። ከእስራቴ በፊትና በኋላም የጻፍኳቸውም መጻሕፍት ለሕትመት በቅተዋል። ሌሎቹም ሕትመት እየተጠባበቁ ናቸው።

(የጋሼ አበራ “ድርሳነ ህይወቴ” መጽሐፍ ከታተሙት መጻሕፍቶቹ ውጪ የሕግ ነክ የምርምር ጹሁፎች እና ሌሎች የምርምር ስራዎቹን ዝርዝር ይዞ በዚህ ተጠቃለለ።)
ታሪኩንና ስራዎቹን በጥያቄ መልክ አቅርቤ መልሱን የወሰድኩት ከዚሁ “ከድርሳነ ህይወቴ” መጽሐፍ ነበር። “ድርሳነ ህይወቴ” ልዩ ልዩ ፎቶዎችን ጭምር ያካተተ ባለ 248 ገጽ መጽሐፍ ነው። ብልህ ሰው በዚህ በኔ ጽሁፍ ሳይገታ መጽሐፉን አግኝቶ ሊያነብ እንደሚችል አምናለሁ።
አልጨረስኩም፤ በዚሁ አንጠልጥዬ ብተወው ዶ/ር አበራ የት ደረሱ ማለትዎ አይቀርም። አሁን ጋሽ አበራ የት ደረስክ? ብዬ አልጠይቀውም፤ ብጠይቀውም አይመልስም። ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው ያም እኔው መናገር አለብኝ።
ዘመዴን ስስመው
ጉንጨ ቢሻክረው
እኔንም ሻከረኝ
ዕድሜ መለስለሱ ማብቃቱ ታወቀኝ።
ግጥም - ደበበ ሰይፉ
ከጋሼ አበራ የህይወት ውጣ ውረድ ትረካ ማህል የራሴን ትዝታ ይዤ ጣልቃ መግባት አልፈለኩም። በልጅነቴ ስለሱ ያለኝን ትውስታ ተናግሬያለሁ። ከመታሰሩ በፊትም ሆነ በኋለኛው ዘመን አገኘው ነበር። ሰው አክብሮቱ፣ ትህትናውና በጎ ምግባሩ ምንግዜም አይረሳኝም። እነዛን የኔም ሀብቶች እንዲሆኑ ጥሬያለሁ። በመጠኑም ተጋርቻለሁ። እውቀቱን ግን በማንኪያ እንኳን ቆንጥሬ ልወስድ አልቻልኩም እሱ፤ እንዳመለጠኝ ቀረ።
ስዊድን በስደት ከመጣሁ ጥቂት ወራት በኋላ ጋሼ አበራ ለህክምና እንደመጣ ሰማሁ። እንዴ! በደህና ጥየው የመጣሁት ሰውዬ ምን ነካው? ደነገጥኩ። ከነበርኩበት የስዊድን ሰሜናዊ ክፍል ወደ ስቶክሆልም ገስግሼ ገባሁ።
ጋሼ አበራን ያገኘሁት ባልጠበኩት ሁኔታ ነበር። ሸበቶ ፀጉሩ ጎፍሯል፣ ሰውነቱ ሸሽቶት ሄዷል፣ ጉንጮቹ ሟሸዋል፣ ቅላቱ የለም፣ ቁመቱ ሳይቀር አጥሮ ታየኝ። ታሟል! ጋሼ አበራ ታሟል!። “ዓለም ለግለሰብ ደንታ የላትም” ሲባል የሰማሁ ይመስለኛል ወይም አንብቤያለሁ። አዎን! ዓለም ለግለሰብ ደንታ የላትም።
የኛስ ሀገር ብትሆን የዓለም አንዱ ክፍል አይደለች? እንደውም በሷ ይብሳል። የለፉላትንና የደከሙላትን አትወድም። ልጆቿን በገዛ ልጆቿ እጅ አንቃ የምታስገድል ሀገር ነች። እነ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አለጥፋታቸው ተንጠልጥለውባታል። እነ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ በጥይት ተቆልተውባታል። ከዛስ ወዲህ ቢሆን እነ ፕሮፌሰር አሥራት በእስር ተንገላተው ሞተውባታል። እነ አሰፋ ማሩ በጠራራ ፀሐይ ምድሯ ላይ ተዘርግተውባታል። እነ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ በእስር ቁም ስቅል አይተዋባታል። አሁንም እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ እነ ርዕዮት ዓለሙ፣ … በመከራ ጎጆ ተከርችሞባቸው ይገኛሉ።
ጋሼ አበራም የገጠመው ይሄው ነው። ከወጣነቱ ጀምሮ ለሀገሩ ሰራ። በውጪ ሀገራት ተመላለሰ። ለህዝብ ቅርስ ሆነው የሚቀሩ መጻሕፍትን ጻፈ። ተርጎመ። በማኅበራዊ አገልግሎቶች ተሳተፈ። ለዚህ ሁሉ እንግልቱ ግን ታላቁ ስጦታው የስምንት ዓመት እስራት ነበር።
ያ እስራት ብዙ ጎድቶታል። ጤናውን አቃውሶታል። ትዳሩን በትኖበታል። ኑሮውን አናግቶበታል። ልጆቹን በሚፈልገው መልክ ለመቅረጽ ሳይችል እንዲቀር አድርጎታል። ሆኖም ከእስር ወጥቶም እንደገና ለሀገሩ መስራቱን አላቋረጠም። ሀገሩ እንዲያ በድላው አላቄመባትምና። ያመለጠውን ትምህርት እንኳን አሳዶ ይዞ ዶ/ር እስከመሆን ደርሷል። በመጨረሻ ግን ተሸነፈ፤ የመጨረሻውን ሀያል እንቅልፍም አንቀላፋ። ወደ አባቶቱ መቃብርም ወርዶ ተከማቸ።
እናቴ ዛሬም በህይወት አለች። በጨዋታ ማህል ጋሽ አበራን ታነሳለች። ዛሬም ያንኑ መጽሐፍ እንዳነክ ነህ? ትለኛለች። (ኮንፒዩተር የሚባል ጉድ ማነቄን አለማወቋ በጃት) አዎን! ምን ላድርግ ብለሽ ነው? … አዬ! ጽ … ያ ልጅ አበራም እንዲሁ ነበር። እሱኑ እንዳገላበጠ ነው የኖረው፤ ሲበላ እንኳን ያነብ ነበር። መቼም ማንም መጽሐፍ ይወዳል ቢሉኝ አላምንም፣ የልጅ አበራ ልዩ ነበር። ይሄ የናቴ የዘወትር አባባል ነው።
እናቴ ልክ ነበረች፤ ጋሼ አበራ በመጨረሻው ሰዓት ሁለት ለሕትመት የደረሱ መጻሕፍቶቹን በእጁ እንደጨበጠ ነበር ይችን ዓለም የተሰናበታት።
(ተፈፀመ)

No comments:

Post a Comment