Friday, June 28, 2013

በአዲስ አበባ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ የተመዘገበው ህዝቡ ቁጥር መንግስት በቅርቡ ካወጣው አዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር ጋር የማይጣጣም ነው ሲሉ አንድ ባለሙያ ገለጹ

ኢሳት ዜና :-በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ቆጠራ ኮምሽን ሰሞኑን የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር 2 ሚሊዮን 900 ሺ መሆኑን ቢገልጽም፣ በ10 – 90 እና በ20 – 80 እየተባለ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተመዘገበው ህዝብ ቁጥር ኤጀንሲው ያቀረበው አሀዝ  ትክክል አለመሆኑን የሚያሳይ ነው በማለት አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የጠየቁ ቀድሞ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ባለሙያ ለኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ ገለጹ።
ባለሙያው እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ መንግስት ከ800 ሺ እስከ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ለቤት ፍለጋ እንደሚመዘገቡ ከገለጸ የከተማዋ ነዋሪ የዚህን አሃዝ ከ4 እስከ 5 እጥፍ ሊሆን ይችላል ማለት ነው ብለዋል።
መንግስት እስከሁን ከ700 ሺ ህዝብ በላይ እንደተመዘገበ፣ በሚቀጥሉት ቀናትም ተጨማሪ 100 ሺ ህዝብ ሊመዘገብ እንደሚችል መግለጹን ያወሱት ባለሙያው፣ ቀደም ብሎ ቤት ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከ300 እስከ 600 ሺ የሚገመቱ ከሆነ በአጠቃላይ በከተማው ከ1 ሚሊዮን 100 ሺ እስከ 1 ሚሊዮን 400 ሺ ሰዎች ቤት ይፈልጋሉ ማለት ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ አንድ ሰው ከ3 እስከ 4 ልጆች ሊኖሩት እንደሚችል የገለጹት እኝህ ባለሙያ በዚህ ስሌት መሰረት የከተማው ህዝብ ቢያንስ ከ3 ሚሊዮን 500 እስከ 5 ሚሊዮን 500 ሺ ሊደርስ ይችላል ብለዋል።
አሀዙ በቤት ምዝገባ ያልተካተቱትን እጅግ ደሀ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም አድራሻ አጥተው የተቀመጡትን ነዋሪዎች ካካተተ ከተማው ህዝብ ብዛት ከ5 ሚሊዮን ሊበልጥ እንደሚችል ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ መስተዳድር የከተማውን ህዝብ ቁጥር ከ5 ሚሊዮን በላይ አድርጎ ማቅረቡ ትክክል ሊሆን እንደሚችል፣ ስህተቱ ያለው ማእከላዊ ስታትስቲክስ ባወጣው መረጃ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የህዝብ ቁጥርን መቀነስ ለምን አስፈለገ የተባሉት ባለሙያው አንዱ ምክንያት በመስሪያ ቤቱ አቅም ችግር ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ፖለቲካዊ ምክንያት ሊኖረው ይችላል ሲሉም አክለዋል። ክልሎች የፌደራል መንግስቱን የገንዘብ ድጎማ የሚያገኙት በህዝባቸው ቁጥር መጠን በመሆኑ ትክክለኛ የህዝብ ቁጥር ካልታወቀ በማህበራዊ አግልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል።

No comments:

Post a Comment