Tuesday, June 11, 2013

በሙስና የታሰሩት የጉምሩክ አቃቤ ሕግ፣ ቀብረውት የነበረ ከ1ሚልዪን በላይ ብር መገኘቱ ተነገረ

corruption

ኢሳት ዜና:-በሙስና ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ህግ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ማርክነህ አለማየሁ ቀብረውታል የተባለ ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ መገኘቱ ታውቋል።
ጉዳዪን የሚከታተለው የምርመራ ቡድን እንዳስታወቀው ከሆነ፣- አቶ ማርክነህ አለማየሁ በወንድማቸው አማካኝነት ለመሰወር አቅደው የቀበሩት አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ዘጠና ሺ ብር የተገኘው ወላይታ ሶዶ፣ ወራንዛላሸ በተሰኘች ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው።
ይኸው ገንዘብ ተገኘ የተባለው ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም  ነው።  ገንዘቡ አቶ ማርክነህ በኃላፊነት ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ ባለመመስረት፣ እንዲሁም መከፈል የሚገባቸውን የመንግሥት ገቢ እንዳያስገቡ በመመሳጠር የሰበሰቡት ነው» በማለት የምርመራ ቡድኑ አስታውቋል።ካሁን ቀደም የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ገብረዋህድ ገብረጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት ዉስጥ፣ 200ሺ የኢትዮጵያ ብር፤ 26ሺ ዩሮ፤ ፓዉንድና የተለያዩ አገራት የገንዘብ ኖቶች፤ መገኘቱ ይታወሳል።
በአቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ 3ኛው ተከሳሽ የሆኑት አቃቤ ሕግ ማርክነህ አለማየሁ የታሰሩት፣ ከአንደኛው ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታ እና ከሁለተኛው ተከሳሽ አቶ እሸቱ ወልደሰማያት ጋር በማበር፣- ሕገ-ወጥ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በ2001 ዓ.ም በአራጣ ብድር በፍርድ ቤት የተመሰረተን ክስ በስልጣናቸው እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው። መርማሪ ቡድኑ አገኘሁ ያለውን ገንዘብ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልተቻለም።

በአፋር ፌደራል ፖሊሶች ከህዝቡ ጋር ሲታኮሱ ዋሉ

ኢሳት ዜና:-በትናንትናው እለት የ20 አመቱ ወጣት የሆነው ሙሀመድ ካይብ የፌደራል ፖሊስ አባላት በቅርበት ባሉበት በኢሳዎች መገደሉን ተከትሎ፣ አፋሮች ገዋኔ ወለጌሊ እየተባለ በሚጠራ ስፍራ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ዛሬ ሲታኮሱ ውለዋል። ስቱዲዮ እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ተኩሱ አለመቆሙን ለማወቅ ተችሎአል።
ነዋሪዎች በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ የከፈቱት ፣ ፖሊሶቹ ሆን ብለው ሁለቱን ብሄረሰቦች ለማጋጨት እየጣሩ ነው በሚል ምክንያት ነው። ከሳምንት በፊት በዚሁ አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ በተጠየቁበት ጊዜ ተኩስ በመክፈታቸው ፖሊሶቹ አካባቢውን ለቀው መሄዳቸውንና ግጭቱ መብረዱን መዘገባችን ይታወሳል። ዛሬ የተፈጠረው ግጭት ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው ግጭት ጋር እንደሚያያዝ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በግጭቱ ምን ያክል ሰዎች እንደቆሰሉ ወይም እንደሞቱ ለማወቅ አልተቻለም። በጉዳዩ ዙሪያ የአፋር ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

በማዳበሪያ እዳ ለስደትና ለእንግልት ተዳርገናል ሲሉ አርሶ አደሮች ተናገሩ

ኢሳት ዜና:-በሺንዲ ወንበርማ ወረዳ የማንችለውን ውዝፍ የማዳበሪያ እዳ እንድንከፍል በመገደዳችን ለስደትና እንግልት ተዳርገናል ሲሉ በርበሬ አምራች አርሶ አደሮች ተናግረዋል ፡፡
በመንግስት በታጠቁ ሀይሎች ሀብት ንብረታችን ተዘርፎና የቤታችን ቆርቆሮው ተገፎ ተወስዶብናል ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አርሶ አደሮች፣  ዛሬ ቤት ንብረታችንን ጥለን ቤተሠባችንን በትነን ለስደት ተዳርገናል ብለዋል።
በአየር ንብረት መዛባት ችግር በደረሰብን አደጋ ምርታችን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ በመቻሉ ምክንያት ወዝፍ የማዳበሪያ እዳ መክፈል አልችል በማለታችን እንግልቱ ደርሶብናል ሲሉ አማረዋል፡፡
መንግስት ሊደግፈን ሲገባ   ማሳደዱና መንገላታቱ ከፉኛ አሳዝኖናል ያሉት አርሶአደሮቹ ችግራቸው ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ መንግስት እንዲያሻሽልላቸውም ተማፅነዋል፡፡
የበርበሬ ምርት በቀላሉ ለብልሽት የሚዳረግ በመሆኑ በደረሰው የአየር ንብረት መዛባት ምርታችን በሜዳ ስለቀረ እዳችንን መከፈል ተስኖናል ያሉት አርሶ አደሮች ይህ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ መንግስት ህዝቡ ላይ ባሳደረው የእዳ ጫና ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር የሚያወጣው አርሶ አደር ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ብለዋል፡፡
ሺንዲ ወንበርማ ወረዳ  በበርበሬ አምራችነቷ ብቻ ሳይሆን በምርጥ ዘር ብዜት ማዕከልነቷ ወሳኝ የሚባል ሀገራዊ ሚና አላት።  ተፈጥሮ ባመጣው ክስተት እዳቸውን መክፈል ያልቻሉ አርሶ አደሮች በመንግስት ለእስርና ለስደት መዳረጋቸው፣  የስንዴም ሆነ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማባዛት  ወደ ኋላ እንዲሉ እንዳደረጋቸው  አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ።
ከማዳበሪያ እዳ ጋር በተያያዘ በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎችም ከፍተኛ የሆነ ሮሮ እየተሰማ ነው። መንግስት በግዴታ የሚያከፋፍለውን ማዳበሪያ በመውሰድ እዳ ውስጥ የገቡ የደቡብ ክልል አርሶ አደሮች ቤት ንብረታቸውን እየሸጡ እስከ መሰደድ ደርሰዋል።
የኢትዮጵያን ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡት የገዢው ፓርቲ ኩባንያዎች መሆናቸው ይታወቃል። የኢህአዴግ ካድሬዎች  በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ገበሬው ያለበትን የማዳበሪያ እዳ በማስከፈል ነው። በማዳበሪያ  እዳ ምክንያት  ቤት ንብረታቸው አፍረሰው የተሰደዱ አርሶ አደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በግብርና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት መናገራቸው ይታወቃል። መንግስት የገዢውን ፓርቲ ኩባንያዎች ጥቅም ከማስጠበቅ ውጭ ችግሩን ለመቅረፍ እስካሁን መሰረታዊ ሆነ እርምጃ ሲወስድ አልታየም።

ፓዌ ወደ ልዩ ወረዳነት እንድትመለስ የጠየቁ ነዋሪዎች እንግልት እንደደረሰባቸው አስታወቁ

ኢሳት ዜና:-በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የሚኖሩ ነዋሪዎች  ፓዌ  በፊት ትጠራበት ወደነበረው ልዩ
ወረዳነት እንድትመለስ በመጠየቃቸው ከፍተኛ እንግልት እና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በወረዳዋ የሚኖሩ ወጣቶች በጋራ እንደገለፁልን ከ1977 ዓ.ም በፊት ከሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በሠፈራ መጥተው ፓዌ ወረዳ ላይ የቆዩ ሲሆን በ1983 ዓ.ም በአካባቢው ከሚኖሩ ጉምዝ፣ ሺናሻ፣ ርታ፣ ማኦ እና ኮሞ ተወላጆች ጋር እርስ በርስ የተፈጠረውን ግጭት ለማስማማት በወቅቱ በነበሩት ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ ውሣኔ መሠረት ፓዌ ልዩ ወረዳ እንድትሆን መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ በክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ አህመድ ናስር አማካኝነት ፓዌ ልዩ ወረዳ መባሉዋ ቀርቶ  ፓዌ ወረዳ ብቻ እንድትባል በመወሰኑና ውሳኔውን ባለመቀበላችን የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ተሰብስበን ጥያቄ ብናቀርብም ፣ አቶ ገዱም  መኢአድ ፓርቲን ምረጡ እንጂ እንደ እናንተ አይነት አማራ አናውቅም በማለት ልዩ ወረዳ መሆኑን ሣይቀበሉት መቅረታቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡
አማራ ክልልን ከቤኒሻንጉል በሚያዋስነው ኬላ ላይ ፓዌ ልዩ ወረዳ የሚል መታወቂያ ይዘው የተገኙ  ተወላጆች ላይ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባ በማድረስ ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን መታወቂያ ካርድ ተቀበለው የሰበሰቡ ሲሆን ልዩ ወረዳ የሚል መታወቂያ ይዞ በክልሉ ሆቴል ቤቶች አልጋ መያዝ እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡
ፓዌ ልዩ ወረዳ በነበረችበት ወቅት ከሁሉም ብሄር የተወጣጡ አስተዳዳሪዎች ሲያስተዳድሩዋት  እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪዎች በአዲሱ ውሳኔ መሰረት  የወረዳው ሕግ አስፈፃሚ የአንድ ብሄር ተወላጆች ብቻ እንዲሆን መደረጉ እየደረሰብን ያለውን ጫና አባብሶብናል ብለዋል። የፌዴሬሽን ም/ቤት አስቸኳይ መፍትሄ ይሰጠን ሲሉም ጠይቀዋል። ፔዌ በደርግ ዘመን የተጀመረውን የጣና በለስ ፕሮጀክት ምክንያት በማድርግ ከተለያዩ አካካቢዎች ተሰባስበው የሄዱ ኢትዮጵያውያን የመሰረቱዋት ከተማ መሆኑዋ ይታወቃል።

የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ብቻ መሸፈን ወይም ዳር ማድረስ አይቻልም ተባለ

ኢሳት ዜና:-በሥራ ዓለምም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች የሠሩትና የፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት  አምባሳደር ሀይሉ ወልደጊዮርጊስ  ይህን የገለጹት እሁድ ለህትመት ከበቃው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በ ዓባይ ግድብ ዙሪያ  ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።
“ የ ዓባይ ውሀ በህግ ላይ የሚያቀርበው ፈተና” በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ  መጽሐፍ ያሳተሙት አምባሳደር ሀይሉ ለህዳሴው ግድብ እስካሁን ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ገና ከ 5 ቢሊዮን ብር እንዳላለፈ አመልክተዋል።
የግድቡ ግንባታ የሚጠይቀው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ነው  ያሉት አምባሳደር ሀይሉ፤ይህን ያህል ገንዘብ በራሳችን ለማዋጣት ያዳግተናል ብለዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ  የ ዓባይን ግድብ ያለምንም የውጪ እርዳታ በራሳችን እንሠራዋለን በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።
ያለ እርዳታ ግድቡ የማይቻል መሀኑን ያብራሩት አምባሳደሩ፤ ግብፅ የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት ተቀብያለሁ ብላ ካረጋገጠች፣ ኢትዮጵያ የውጭ ዕርዳታ ታገኛለች የሚል አመለካከትና እምነት ስላላት ነው >>ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፦<<ግድቡ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ ቢውል ግን ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ግብፅና ሱዳንም የጥቅሙ ተጋሪ ይሆናሉ ።እነሱ ግን ይህ በጎ ጐኑ አይታያቸውም፡፡ የግብፆች ትልቁ ጥርጣሬያቸው ኢትዮጵያ በሕዝቡ መዋጮ ብቻ የግድቡን ግንባታ የማጠናቀቅ ወይም ዳር የማድረስ አቅም ስለሌላት ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ከሌሎች አገሮች በስውር ዕርዳታና ብድር ልታገኝ ትችላለች የሚል ነው>>ብለዋል-።
ስለሆነም ይህንን ለማጨናገፍ ሲሉ የማስፈራራት ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ እና ለዚህም ተግባራዊነት መልዕክተኞቻቸውን ወደተለያዩ አገሮች በመላክ የማግባባት ሥራ እያካሄዱ ስለመሆናቸው የገለጹት አምባሳደር ሀይሌ፤<< ደቡብ ሱዳን እንኳን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንዳትቀበል ወይም እንዳትፈርም ብዙ ተፅዕኖ አድርገውባት ነበር፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐንም እንዲሁ አግባብተዋል፡፡ >>
ከ አምባሳደሩ ገለፃ ለመረዳት እንደተቻለው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ለሚባለው ለግድቡ ሥራ እስካሁን የተዋጣው ገና 6 በመቶ ያህሉ ነው። ይህ ማለት ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ግድብ ገና 94 በመቶ የሚሆነው ወጭ ይጠብቀዋል። የ ኢትዮጵያ ህዝብ በውድም፣በግዳጅም እንዲያዋጣና ቦንድ እንዲገዛ ተደርጎ የተሰበሰው 6 በመቶ ከሆነ አምባሳደሩ እንዳሉት ግድቡን ያለውጪ ዕርዳታ ካለበት ቦታ ብዙም ማንቀሳቀስ አይቻልም።
ከዚህ አኳያ የግድቡ ሥራ መቀጠልና አለመቀጠል የሚወሰነው ኢትዮጵያ እርዳታን ለማግኘት፤ግብጽ እርዳታን ለማስከልከል እያደረጉ ባሉት ትግል እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ።
ESAT

No comments:

Post a Comment