Friday, March 21, 2014

ለአልሙዲ “ማፅናኛ”(ከጋዜጠኛ ተስፋዬ ተሰማ)

March 20/2014

በቅርቡ ባህርዳር ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያ ስፖርት በአል ሼኽ አልሙዲ በክብር እንግድነት ተጋብዘው ነበር። የበአሉን መክፈቻ በቲቪ ስከታተል አንድ ጥያቄ ወደ በአእምሮዬ መጣ። አልሙዲንን የክብር እንግዳ አድርጐ መጋበዙ ለምን አስፈለገ?..ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። “የገዢው ፓርቲና የባለስልጣናቱ ታማኝ ወዳጅ ስለሆኑ፣ በባህርዳሩ ስታዲየም ግንባታ ድርጅታቸው ስለተሳተፈ ወይም ሼኹ ለስፖርት ያላቸውን ፍቅር በማየት..” የሚሉ ነገሮችን መደርደር ይቻላል።

በእኔ ግምት አልሙዲ በባህርዳሩ በአል በእንግድነት የተጋበዙት በሰሜን አሜሪካ ስፖርት በአል ላይ ስለተዋረዱ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት የፈጠርዋት ማፅናኛ ትመስለኛለች። ባለፈው አመት እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በአንድ ሳምንት ሁለት የኢትዮጵያ ስፖርት በአል ተከበሮዋል። አንድኛው በሼኽ አልሙዲና የዳይስፖራውን ማንነትና ፍላጐት ባልተገነዘቡ ወዳጆቻቸው የተዘጋጀ ነበር። በነዚህ ወገኖች ግምት “ዳያስፖራው በተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ካድሬዎች የሚሽከረከር የዋህ ህዝብ” አድርገው ይወስዱታል።

 አሜሪካ ሀገር ከኅይለስላሴ ጀምሮ በደርግ ጊዜ ከዛም በኋላ የመጣው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ (በምንም መንገድ አሜሪካ ይምጣ) ለዘሩ፣ ለጐሳው ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነቱ ጥልቅ የሆነ ፍቅርና ክብር አለው። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግን የዘር ፖለቲካ አይደግፍም። ከደጋፊዎቹም ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ የገባው በዚህ አገር ወዳድ አቋሙ ነው። ይህ እውነት ያለገባቸው አልሙዲና ተከታዮቻቸው በስፖርቱ አስታከው ዳያስፖራውን እንቆጣጠራለን በማለት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ቢከሰክሱም አልተሳካላቸውም። ባዶ ስታዲየም ታቅፈው ነው የቀሩት። ሁለተኛው ኢ.ኤስ.ኤፍ.ኤን የሚባለው ኢትዮጵያዊ ፌዴሬሽን የነሱን ያክል ገንዘብ ሳይኖረው በርካታ ህዝብ ከጎኖ ማሰለፍ ችሎዋል። እንዲያውም ስታዲየሙ ሞልቶ ሰው እስኪመለስ ድረስ። በዚህ በአል ከፍተኛ የሆነ የአንድነትና የአገር ፍቅር ስሜት የታየበት፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ በብዛት የተውለበለበበትና ያሸበረቀበት፣ ሰዎች ከብሄራቸው ይልቅ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያገነኑበት ትልቅ በአል ነበር።

ባዶ ስታድየም የታቀፉትና አፍረው በውርደት ለተመለሱት አልሙዲ የባህርዳሩ እድል በማፅናኛነት ተሰጣቸው። ኢትዮጵያዊያን በነፃነት በሚኖሩበት አሜሪካ ግን አልሙዲ በገንዘባቸው የህዝብን ድጋፍ መግዛት አይችሉም። በገንዘብ ምንም ማድረግ እንደማይችሉም ሊያውቁት ይገባል።

ሴቶች ለዓገራቸው ነጻነት የሚያደርጉትን ተሳተፎ በመደገፍ ኢትዮጵያ ዓገራችንን ካለችበት ስቃይ እንታደጋት....!!!

ራሄል ኤፍሬም
ቀደም ካለው ከሴቶች ተሳትፎ በመነሳት አውን እስካለንበት ጊዜ እንስቶች በፖለቲካው ያላቸውን ትልቅ ሚና ላነሳ ወዳለው።
በሁሉም የማህበራዊ ህይወት ዘርፎች ውስጥ የኢትዮጵያ ሴቶች የሚጫወቱት ጉልህ እና ወሳኝ ሚና ያላቸው ቢሆንም ሃገሪቱ ባላት ባህል፣ ታሪክ፣ እና ፖለቲካዊ ስርአት ምክንያት በሁለንተናዊ ማህበረሰብ እድገት ያደረጉት አስተዋጽኦ ተገቢውን ትኩረትና እውቅና አላገኘም። በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ አግላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበረሰባዊ ህግና ደንቦች ምክንያት ሴቶች የልፋታቸውን ውጤት ሳያገኙ ቆይተዋል። እንደሚታወቀው ሴቶች የዓለማችን ግማሽ አካል እንደመሆናቸው መጠን ተገቢውን ስፍራ ሳይሰጣቸው ነገር ግን በዘልማድ በማህበርሰቡ ውስጥ ሴቶች በዓገር፣ በእናት፣በሚስት ይመሰላሉ። እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ከታዋቂ ወንድ በስተጀርባ ጠንካራ ሴት እንዳለች ቢነገርም በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ተገቢ ቦታ እና እውቅና አልተስጣቸውም። ቀደም ባሉ ጊዜያት ሴትልጅ ከቤት ስትወጣ ነውር በሆነበት ወቅት አጠቃላይ የቤት ውስጥ ስራ ሃላፊነት በተለይም ለወንዶች ምግብ አዘጋጅቶ የመጠበቅ ግዴታ የሷ ሲሆን፣ከማጀት ስራዋ በተጓዳኝ ዓገር ተረካቢ ዜጋን የማምረት እና የማሳደግ ጫናው የዚችው የምስኪኗ ሴት ሓላፊነት ነበር ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች እናቶች ቢኖሩም ባለው ማህበረሰባዊ አፈና ምክንያት በሴቶች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ጉልህ ሚና ሳይጫወት ቀርተዋል። እነዚ ቆራጥ እና ጀግና ታሪካዊ ሴቶች በወቅቱ የነበረውን ዋላቀር  አስተሳሰብ በመቋቋም በድፍረት እና በጀግንነት ከወንዶች በስተጀርባ በመሆን ላገራቸው ነጻነት ያላቸውን ተሳትፎ በቆራጥነት አሳይተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜም የሴቶች እንቅስቃሴ እየተሻሻለ የመጣበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የግል ጥቅሙን በማራመድ ላይ በሚገኘው በዚህ አረመኔ መንግስት ምክንያት ዓገራቸውን ትተው በስደት ላይ የሚገኙ እና የትውልድ ዓገራቸው ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጋ  በመቆጠር በስቃይ ላይ የሚገኙ  ቆራጥ ሴት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓረቲ አመራሮች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ይህም የሆነበት ምክንያት በአገራቸው የፖሊቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረስባዊ ሁኔታ በጉልህ መብቶቻቸውን ለመተግበር እና ስለ መብቶቻቸው ተሟጋች እንዲሆኑ ስለማይፈቅድ ከውጭ በመሆን ባገራቸው ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ዛሬ በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ  የሴቶች ተሳትፎ እድገት እንዲጨምር ትልቁን የህይወት መሰዋትነትን ከፍለው ያለፉ እንዲሁም እየከፈሉም ያሉ ጀግና እንስቶች ለኛም ሆነ ለዓለም ትልቅ ምሳሌወቻችን ናቸው ።

በኢትዬጽያ ውስጥ የፖለቲካና ሲቪክ መብቶች ከሆኑት ውስጥ የመናገር፣ የመጻፍ፣ እና በአጠቃላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጸ መብት በሌለበትና በተገደበበት ሁኔታ ገዢው መንግስት መስማት የሚፈልገውን ብቻ መናገር እና መጻፍ ግዴታ በሆነበት ቦታ ላይ መስዋእትነት የሚከፍሉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ለዓገራቸው፣ ለወገኖቻቸው እና ለነጻነታቸው በመቆም አምባገነናዊ ስርአትን በመታገል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ። ለህዝብ ደህንነትና መብት ደንታቢስ የሆነው  በስልጣን ላይ የሚገኘው  ይህ ክፉ መንግስት ሴቶች እህቶቻችን እና ወገኖቻችን በነጻነት በመናገራችው፣በመጻፋቸው ፣በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመቃወማቸው እና የሚፈልጉትን ፓርቲ በመምረጣችው ብቻ አሸባሪ በማለት እስር ቤት በማጎር ይገኛል።
 ከነዚህ ጉልህ ሚና ከሚጨወቱ ሴቶች እህቶቻችን መካከል በሰብአዊ መብት ተሟጋችነት እና በጋዜጠኝነት እንዲሁም በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙትን እንስቶች እንዳሉ እና ከነዚህም መካከል እንደ ነብርቱካን ሜዴቅሳ እና እንደ  ሪዖት አለሙ ወ.ዘ.ተ ያሉ ለኛ ትልቅ ምሳሌ የሚሆኑን ጀግና ሴቶች ናቸው ።

የጀግኖቻችንን ምሳሌ በመከተል የአለም አቀፍ ሴቶች ቀን ማርች  8  በተከበረ ማግስት በአዲስ አበባ በተደረገ የሩጫ ውድ ድር  ከተሳተፉ ሴቶች መካከል አጋጣሚውን በመጠቀም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ እና በማህበራዊ ኑሮ የ ሚደርስባቸውን አፈና እና ጭቆና በማሰማት መብታቸውን ለማስከበር ጠንካራ ቋም እንዳላቸው ያሳዩበት አጋጣሚ ነበር። ይህም ክስተት ሴቶች እህቶቻችን ልክ እንደ ቀድሞው አሁንም የወገኖቻችንን ድምጽ ማፈን እና ማሰቃየት የለት ልማዱ ያደረገውን የወያኔ መንግስት የሚያደርስባቸውን ከባድ ጫና ወደጎን በማድረድ ድምጻቸውን ከማሰማት እና ችግሮቻቸውን ከማሳወቅ ወደዋላ ሳይሉ  ከፊታቸው የተደቀነ መሳሪያና የሚደርስባቸውን እስር ሳያስፈራቸው አምባገነናዊ ስርዓቱ እያደረሰባቸው ያለውን ጭቆና በተቃውሞ ገልጸዋል።

ሴቶች ለዓገረቸው በፖለቲካው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና በሚጫወቱበት በዚህ ወቅት አበረታች እና ተስፋ የሚጣልባቸው አዲስ ጀግና እና ለመብታቸው ተሟጋች ትውልዶች እየመጡ እንዳሉ በተግባር እያየን ነው።  ከጎናቸው በመቆም የህቶቻችን ድምጽ እንዲሰማ አስተዋጽዖ በማድረግ ያሉበትን ስቃይ እና መከራ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሰማት በወያኔ መንግስት ላይ ውግዘትና ውርደት ማድረስ ተገቢ ነው። ዓገራችን ካለችበት ከባድ ችግር ለማውጣት አንዱ እና ዋንኛው የሴቶች ተሳትፎ እንደመሆኑ መጠን ያላቸውን የመስራት ትልቅ ችሎታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለዓገራቸው ነጻነት የሚያደርጉትን ተሳተፎ በመደገፍ ዓገራችን ካለችበት ስቃይ እንታደጋት።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ..!!